Monday, October 10, 2011

አጋፔ - መንፈሳዊ ፍቅር ምንድን ነው?


የእውነተኛ ፍቅር ምክንያቱ እራሱ ፍቅር ብቻ ነው። አፍቃሪው ከተፈቃሪው በምላሽ የሚጠብቀው ነገር የለም። ተፈቃሪው ምንም አይነት ሕፀፅ /ጉድለት/ ቢኖርበት አፍቃሪው በሚሰጠው ፍቅር አይቆጭም። ተፈቃሪው የተሰጠውን ፍቅር አቃሎ ወይም ዘንግቶ በደል ቢበድል እንኳ አፍቃሪው ልፋቴ ከንቱ ቀረ ብሎ አይቆጭም። ፍቅር መስጠትን እንጂ መቀበልን ሂሳብ ውስጥ አያስገባምና። አፍቃሪው ሁል ጊዜ የሚጨነቀው ስለ ተፈቃሪው እንጂ ስለ እራሱ አይደለም።

ይህን ፍቅር የምንማረው እራሱ ፍቅር ከሆነ ከእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር አስቀድሞ ፍጥረታትን የፈጠረው ፍቅሩ አገብሮት ነው። በባህርዩ ምስጉን የሆነ አምላክ ክብሩ በእርሱ ብቻ እንዳይቀር ስለወደደ ብቻ ነው ፍጥረታትን የፈጠረው እንጂ በፍጥረቱ ለመጠቀም አይደለም። እርሱ ፍጡራን ሲያመሰግኑት ክብር የሚጨመርለት ወይንም ባያመሰግኑት ክብሩ የሚጐልበት አይደለም፤ በባህርዩ ምስጉን ነውና። በአርአያውና በአምሳሉ የተፈጠረው የሰው ልጅ በክብርና በተድላ ከሚኖርበት ቦታ እንዳይወጣ ምን ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስጠንቅቆ የመከረውም ስለሚያፈቅረው ነው። ትዕዛዙን ተላልፎ ሕጉን ጥሶ ሲሸሸግም ሊፈልገው የመጣ፣ በኋላም ይቅር በለኝ ብሎ ቢፀፀት ይቅር ሊለው ቃል ኪዳን የገባለት፣ ቃልኪዳኑንም ጠብቆ በጊዜው የፈፀመለት እርሱ የፍቅር አምላክ ስለሆነ ነው። ለሰው ልጅ ድኅነት የሚያስፈልገውን መስዋዕትነት ለመክፈል ሰው እስከመሆን ደርሶ እራሱን ዝቅ ሲያደርግ ከክብሩ እንደመዋረድ ያልቆጠረው ከፍቅሩ የተነሳ ነው። ሊያድነው በመጣው በሰው ልጅ እጅ መከራን ሲቀበል፣ ሲገረፍ፣ ሲጐተት፣ እርቃኑን ሲሰቀል፣ በመስቀል ላይ እንኳን ውሎ ሲዘበትበት፣ ተጠማሁ ሲል ሆምጣጤ ሲያጠጡት፣ በተሰቀለበት ጐኑን ሲወጉት… ሁሉ የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ያሰኘው ይህ ፍቅር ነው። ይህ ነው ስሜት ያልተቀላቀለበት፣ ጊዜያዊ ጥቅም ያላገበረው እውነተኛ ፍቅር ማለት ።

በትዳር ውስጥ ሊኖር የሚገባውም መዋደድ ይህን አምላካዊ ፍቅር ከመረዳት የሚመነጭ ነው። ሁለት ተጋቢዎች የሚቀራረቡበት ስሜት ወይም የሚጋሩት ሁለቱም የሚፈልጉት “ጥቅም” ሊኖር ይችላል። ይህ ግን ለትዳር አስተማማኝ መሠረት ሊሆን አይችልም። ትዳሩ ሊፀና የሚችለው በሁለቱ ተጋቢዎች መካከል እውነተኛ ፍቅር ሲኖር ብቻ ነው። በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ትዳር በፈተና ይፀናል። ሁለቱ ተጋቢዎች አንዱ ለሌላኛው ደኅንነትና ሰላም ስለሚያስብ ‘አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ’ እንጂ መብትን ለማስጠበቅ ከሚደረግ ውዝግብ የነፃ ነው። ተጋቢዎቹ በየግላቸው የነበራቸው መንፈሳዊ ዓላማና ግብ ለማሳካት በጋራ ይተጋሉ። ምንም እንኳን የአንዱ መንፈሳዊ ጥንካሬ ከሌላው የተሻለ ወይም ያነሰ ቢሆንም እርስ በእርስ ይማማራሉ። ሁለቱ እርስ በእርሳቸው ከመዋደዳቸው በፊት አምላካቸውን በፍጹም ሀሳባቸውና በፍጹም ኃይላቸው ሊወዱት ይገባል። ዘወትር ፍቅረ እግዚአብሔርንና ነገረ መስቀሉን እያሰቡ የሚኖሩ መሆን አለባቸው። ለመንፈሳዊ ሰው ሰውን መውደድ መብት ሳይሆን ግዴታ ነው። ይህንን ግዴታውን የተረዳና የፈፀመ ብቻ ነው ትዳር ለሚጠይቀው እውነተኛ ፍቅር ሊዘጋጅ የሚችለው። ሰውን ለመውደድ የሚቸገር ወይም በማህበራዊና መንፈሳዊ ግንኙነቱ ፍቅርን ለመስጠትና ለመቀበል የሚሳነው ሰው እንዴት “አፍቃሪ” ሊሆን ይችላል? ትዳር ስለመሠረትን ብቻ ወይንም ከተቃራኒ ፆታ ጋር ስለተቀራረብን ብቻ ፍቅር ሊይዘን አይችልም። ስለዚህ ሰው ከትዳር በፊት እራሱን መመርመር ያለበት እውነተኛውንና ከጥቅምና ከስሜት የራቀውን ፍቅር ከቤተሰቦቹና ከጐረቤቶቹ ጀምሮ ለማንኛውም በማኅበራዊ ኑሮ ለሚያገኘው ሰው መስጠት መቻሉ ነው። ይህንን ለራሱ ማረጋገጥ ካልቻለ ስለ ትዳር ከማሰብ በፊት ስለ ፍቅር ምንነትና ስለሚጠይቀው መስዋዕትነት መማር አለበት። ይቆየን!